Saturday, June 21, 2014

የእግዚአብሔር መንግስት





የእግዚአብሔር መንግስት

በመፅሀፍ ቅዱስ ውስጥ የእግዚአብሔር መንግስት የሚለው ሃሳብ የእግዚአብሔር ሉአላዊ ሃይልን በሁሉም ፍጥረት ላይ የሚያመለክት ሲሆን የዳኑ ሰዎች ተስፋንም  ጭምር የሚያመለክት ነው፡፡ ይህ ሃሳብም የብሉይም ሆነ የአዲስ ኪዳን ቁልፍ ሃሳብ እንደሆነ መፅሃፍ ቅዱሳችንን ስንመረምር እንመለከታለን፡፡
በዚህ አጭር ፅሁፍ የእግዚአብሄር መንግስት የሚለውን ፅንሰ ሃሳብ በአጭሩ ለመዳሰስ እሞክራለሁ፡፡  የእግዚአብሔር መንግስትን አስመልክቶ ያሉ የተለያዩ አመለካከቶችን በመመልከት  በተለይ በብሉይና በአዲስ ኪዳን ስለ እግዚአብሔር መንግስት ምን አይነት ሃሳብ እንዳለ ለማስረዳት እሞክራለሁ፡፡ በመጨረሻም በአዲስ ኪዳን በተለይም በወንጌላት ላይ በማተኮር የእግዚአብሔር መንግስት እንዴት በሃይል እንደተገለጠ እና እንደተስፋፋ በመዳሰስ በዚህ ዘመን ካለች ቤተክርስቲያን ጋር ለማዛመድ እሞክራለሁ በጥሞና አንብቡልኝ የተሰማችሁን አስተያየትም ፃፉልኝ፡፡




  I.      የእግዚአብሔር መንግስት ማለት ምን ማለት ነው?
የእግዚአብሔር መንግስት ማለት አምላክ በፍፁም ሉአላዊነት ለዘላለም በሁሉም ፍጥረት ላይ የሚገዛበት ስርአት ማለት ነው፡፡ ይህ ስርአት ሁሉንም ፍጥረት የሚያቅፍ ሲሆን በሰማይም ሆነ በምድር ያሉትን እና በፈቃዳቸው ራሳቸውን ለእርሱ የሰጡትንና ከእርሱጋ ህብረት የሚያደርጉትን ያካትታል፡፡( መዝ 103፡19፣ ዳን 4፡3፣ ዮሀ 3፡5-7)
ስለዚህ የእግዚአብሔር መንግስት ማለት
-          አለም አቀፋዊ ነው መዝ 103፡19
-          ዘላለማዊ ነው ዳን 4፡3
-          ቁሳዊ ሳይሆን መንፈሳዊ በመሆኑ ሁሉም ዳግም የተወለደ ሰው የዚህ መንግስት አባል ነው፡፡ ዮሀ 3፡5-7
-          አንድ ሰው የዚህ መንግስት አባል ስለመሆኑ ማረጋገጫ የሚሰጠው መንፈስ ነው፡፡ ሮሜ 8፡16
II.      ስለ እግዚአብሔር መንግስት ያሉ አመለካከቶች
የእግዚአብሔር መንግስትን አስመልከቶ ብዙ አመለካከቶች አሉ፡፡ ከነዚህ ውስጥ አንዳንዶች የእግዚአብሔር መንግስት ማለት መንግስተ-ሰማይ ማለት ነው ስለዚህም በሰማይ ያለ አገዛዝ ነው ብለው ያምናሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ መንግስቱን ከቤተክርስቲያን ጋር ያዛምዱታል፡፡ ስለዚህም የመንግስቱን ስራ ከቤተ-ክርስቲያን ስራ ጋር ተመሳሳይ እንደሆነ ያስተምራሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ መንግስቱን ከሰው ልብ ጋር በማያያዝ መንፈሳዊ ህይወት ነው ይላሉ፡፡ ለዘብተኛ ተብለው የሚፈረጁ ክርስቲያኖች ደግሞ የእግዚአብሔር መንግስትን ከማህበራዊ ህይወት መቃናትና ስኬት ጋር ያዛምዱታል፡፡ በሌላ ፅንፍ ያሉት ደግሞ የእ/ር መንግስት ገና ወደፊት የሚመጣና አይሁዳውያን 1000 አመታት የሚገዙበት ጊዜ ነው ብለው ያምናሉ፡፡ እስካሁን በተመለከትናቸው አመለካከቶች ውስጥ ተመሰሳይነትም ልዩነቶችም አሉ፡፡ በቀጣይ ከመፅሃፍ ቅዱስ በመነሳት የእ/ር መንግስት በብሉይ እና አዲስ ኪዳን ያለውን ሃሳብ በመመልከት ትክክለኛ የሆነውን የመፅሃፍ ቅዱስ ትምህርት ለማስቀመጥ እሞክራለሁ፡፡
III.      የእግዚአብሔር መንግስት በብሉይና በአዲስ ኪዳን
የእግዚአብሔር መንግስት ፅንሰ ሃሳብ የብሉይም ሆነ የአዲስ ኪዳን ቁልፍ ሃሳብ ነው፡፡ አዲስ ኪዳንም በብሉይ ኪዳን አስተምህሮቶች ላይ ተመሰረተ እንደመሆኑ መጠን ሁለቱን ኪዳኖች በማስተያየት ማጥናት እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡
በብሉይ ኪዳን የእ/ር መንግስት ከያህዌ መሪነት፣ ሉአላዊነትና ሃይል ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ይህን ሃሳብ በተለይ ደግሞ በመዝሙረዳዊት ግጥሞች ውስጥ እናስተውላለን( መዝ 22፡28፣ 103፡19፣ 145፡11) በብሉይ ኪዳን የነበሩ አይሁዳውያን በተለይም ክርስቶስ ወደ ምድር በመጣበት ጊዜ የነበሩት የእግዚአብሔር መንግስት መምጣትን በጉጉት ይጠባበቁ የነበሩ ናቸው፡፡ በተለይም መንግስቱ በኢየሩሳሌም እንድትመሰረት ተስፋ ያደርጉ ነበር ለዚህ መንግስት ምስረታም የመሲሁ መምጣት አስፈላጊነትም በሚገባ ተረድተዋል፡፡ ነገር ግን በጊዜው ልእለ ሃያል የነበረችውን የሮምን መንግስት ጥሎ አይሁዳውያንን ሁሉ የአለም ገዢ ያደርጋል ብለው በማመናቸው የኢየሱስን መሲህነት ለመቀበል ተቸግረዋል፡፡ ስለዚህ ጥበቃቸው የምድራዊ መንግስት ምስረታ ነበር፡፡
ብሉይ ኪዳን የሚጠናቀቀው ስለ እግዚአብሔር ቀን ተስፋ በመስጠት ነው፡፡ በተለይም ህዝቡ የሙሴን ህግ እነዲያከብር በማሳሰብና የነብዩ ኤሊያስን መመለስ ተስፋ በመስጠት ጭምር ነው(ሚል4፡1-6)፡፡ ይሁን እንጂ ምድሪቱ ለ400 አመታት ምንም አይነት የነብይ ድምፅ ሳትሰማ አሳልፋለች መጥምቁ ዮሃንስ እከመጣበት ጊዜ ድረስ፡፡ በነዚህ 400 አመታት እስራኤልን ጨምሮ በመካከለኛው ምስራቅ አካባቢ የፋርስ የግሪክና የሮም መንግስታት ተፈራርቀውበታል፡፡ የተለያዩ አዋልድ መፅሃፍት ተፅፈዋል አዋልድ ነብያትም እንዲሁ፡፡ ነገር ግን አንድም እውነተኛ ነብይ አልተነሳም ህዝቡም የእ/ርን ድምፅ አላሰማም፡፡
የዚህ ሁሉ ጥበቃና ጨለማ ዘመን ያበቃው በመጥምቁ ዮሃንስ ድምፅ ነበር፡፡ በመጥምቁ ዮሃንስ የመጣው የእ/ር ድምፅም እጅግ የሚያስደንቅ ነበር ‹‹መንግስተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሃ ግቡ›› የሚል መልእክት፡፡ ዮሃንስም በነብዩ ሚልክያስ የተነገረለት ኤሊያስ ነበር (ሉቃ 1፡17) ፡፡ ዮሃንስ አገልግሎቱን በጀመረ ሰአትም የአገልግሎቱን አላማ ግልፅ አድርጎ አስቀምጦ ነበር፡፡ ይኽውም መንገዱን ለጌታ ማስተካከል ነበር( ማቲ 3፡1-3)፡፡
ከዚህ በኋላ ነው የክርስቶስ ይፋዊ አገልግሎት የተጀመረው፡፡ በሚያስደንቅ ሁኔታ የኢየሱስ አገልግሎትና ትምህርት መሰረታዊና ማእከላዊ ትምህርት የእግዚአብሔር መንግስት ነበር፡፡ ይህም በማርቆስ ወንጌል ምእራፍ አንድ እንደሚከተለው ተቀምጧል፡-
ዮሐንስም አልፎ ከተሰጠ በኋላ ኢየሱስ የእግዚአብሔርን መንግሥት ወንጌል እየሰበከና። ዘመኑ ተፈጸመ የእግዚአብሔርም መንግሥት ቀርባለች ንስሐ ግቡ በወንጌልም እመኑ እያለ ወደ ገሊላ መጣ።

ሌላው አስደናቂ ጉዳይ ጌታ ለሀዋሪያቱ ያስተማረው ፀሎት ነው በማቴ6፡10 ‹‹ መንግስት በሰማይ እነደሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን …›› ብለው እንዲፀልዩ አስተማራቸው፡፡
ከዚህ ሁሉ በኋላ ኢየሱስ የእ/ር መንግስት መቼ እንደምትመጣ በተጠየቀ ጊዜ ግልፅና የማያሻማ መልስ ሰጠ እነዲህ በማለት፡-
ፈሪሳውያንም። የእግዚአብሔር መንግሥት መቼ ትመጣለች ብለው ቢጠይቁት፥ መልሶ፦ የእግዚአብሔር መንግሥት በመጠባበቅ አትመጣም፤
ደግሞም፦ እንኋት በዚህ ወይም። እንኋት በዚያ አይሉአትም። እነሆ፥ የእግዚአብሔር መንግሥት በመካከላችሁ ናትና አላቸው።
 
ስለዚህ በግልፅ ለመራዳት እነደሚቻለው የእ/ር መንግስት በ ክርስቶስ መምጣት ወደ ምድር እንደመጣች ነው፡፡ ታዲያ ምን ቀረ? የቀረው የእግዚአብሔር መንግስት በምድር በሙሉ ሃይል መገለጥ ነው( ዳን2፡44)፡፡ ሁላችንም እንደምንገነዘበው የምድር ነገስታት ሁሉ እስካሁን አልጠፉም ስለዚህ ይህ ገና ሊፈፀም የሚገባው ትንቢት ነው፡፡ በአጭሩ የእግዚአብሔር መንግስት በክርስቶስ መወለድ የመጣች፣ ገና ደግሞ በሙላት የምትገለጥ ነች፡፡
በአዲስ ኪዳን መንግስቱ ሶስት ደረጃዎች አሉት
1ኛ. የመጀመሪያው የአዲስ ኪዳን የእ/ር መንግስት ደረጃ የሚጀምረው ክርስቶስ በምድር በተመላለሰበት ዘመን መንግስቱ በእርሱ ውስጥ በመሆኑ እርሱን በማመንና በመከተል የተጀመረው ነው፡፡ ማቴ 7፡21
2ኛ. ሁለተኛው ደረጃ ደግሞ የክርስቶስ ከሞት መነሳትና ማረግ ውጤት ነው ይህንም ተከትሎ መንፈስ ቅዱስ ወደምድር በመምጣቱ፡፡ ሐዋ 2፡1-47፣ 28፡23-31
3ኛ. ሶስተኛው ደረጃ ገና ያልመጣና በናፍቆት የምንጠባበቀው የዘላለማዊ መንግስት መገለጥ ነው፡፡ሉቃ 9፡12፣ 21፡31፣ 22፡18 ማር 14፡25 ማቴ 13፡40-43.50
የእግዚአብሔር መንግስት መገለጥ በሃዋሪያት ዘመን
የመንግስቱ አጀማመር በድንገት ነበር፡፡ ነገርግን የተገለጠው በሃይልና በስልጣን ነው፡፡ ይህን ሁሉም ወንጌላት በግልፅ ያስቀምጡታል፡፡ በተለይ በሚከተሉት ሶስት ዋና ዋና መንገዶች ተገልጧል
1.   አጋንነትን በማውጣት፡- ሁሉም የወንጌል ፀሃፍት ክርስቶስ በተለያዩ ቦታዎች ያስወጣቸውን አጋንንት ጠቅሰዋል በህዝቡም መደነቅ ስለመሙላቱ
2.   በሽታን በመፈወስ፡- በተመሳሳይም በብዙ ቦታ በሽታንና ደዌን በመፈወስ የመንግስቱን ስልጣን አሳይቷል፡፡ ፈውሱም በተመሳሳይ መንገድ ሳይሆን በተለያያ መነገድ ይገለጥ ነበር፡፡
3.   ድንቅና ታምራትን በማድረግ፡- ኢየሱስ ድንቅና ተአምራትን በማድረግ በተፈጥሮ ሁሉ ላይ ስልጣን እንዳለው አሳይቷል፡፡ በሞትም ላይ ጭምር ስልጣን እንዳለው በማሳየት የመንግስቱን ስልጣንና ሃይል ገልጧል፡፡
በተጨማሪ በሀዋሪያት ዘመንም ይኽው አሰራር በመቀጠል ወንጌል በሃይልና ስልጣን በመግለጥ የመንግስቱን ሃይል በጨለማው አለም ላይ አጋንንትን በስልጣን በማስወጣት፣ ህመምንና በሽታን በመፈወስ እንዲሁም የተለያዩ ተአምራትን በማድረግ ተገልጧል፡፡
ከዚህ ሁሉ በላይ ግን ልብ ልንለው የሚገባው ቁም ነገር ኢየሱስ በተደጋጋሚ ስለ መንግስቱ ያስተማረው ትምህርት ነው፡፡ በአጠቃላይ የእግዚአብርሔር መንግስት ባህሪ ከውጪያዊ ስርአት ይልቅ ውስጣዊ የሆነ ለውጥና በፍቅር የሚገለጥ ስነ ምግባር ነው፡፡

IV.      በዚህ ዘመን ቤተክርስቲያን የእግዚአብሔር መንግስት
ቀደም ብዬ እንደገለፅኩት የእግዚአብሔር መንግስት አሁን በምድር ያለችና ወደፊትም የምትመጣ ነች፡፡ በተለይ ደግሞ በዚህ ዘመን የእ/ር መንግስት ከቤተክርስቲያን ጋር የተቆራኝች እንደሆነ አምናለሁ፡፡ ምክኒያቱም መንፈስቅ ቅዱስ የተሰጠው ለቤተክርስቲያን ስለሆነ፡፡ ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን በየትኛውም ዘመን ልክ በሀዋሪያት ዘመን እንደነበረው የመንግስቱን ሃይልና ስልጣን በመግለፅ ነፍሳትን ከጨለማው መንግስት የመታደግና የመናጠቅ ብርቱ ሃላፈጊነት አለባት፡፡ በዚህም ዘመን ያለች ቤ/ክርስቲያንም ያለባት ትልቁ ሃላፊነት ወንጌልን ለፍጥረት ሁሉ ማድረስ ነው፡፡ በዚህ ሂደትም የመንግስቱ ሃይልና ስልጣን መገለጥ አለበት፡፡ ትልቁ ጥያቄ የሚሆነው ታዲያ ይህ እየሆነ ነው ወይ የሚለው ነው? ይህን ለመናገር በርግጥ አስቸጋሪ ቢሆንም የዚህ ዘመን ቤተክርስቲያ ትኩረት የዳኑ ሰዎች ላይ መሆኑ ለማንም ግልፅ ነው፡፡ ሌላው በዘመናች ቤ/ክርስቲያን የሚስተዋለው ችግር ደግሞ የመንግስቱ ባህሪና ግብረገብ ውድቀት ነው፡፡ ስለዚህ በዚህ ዘመን ቤተክርስቲያን መንግስቱን መንግስታዊ በሆነ ባህሪ፣ ግብረገብ እና ስልጣን በመግለጥ ቤተ ክርስቲያን በምድር ያለችበትን አላማ መፈፀም አለባት፡፡ እርሱም በጨለማው አለም ላይ በማብራት ህዝብን ወደዚህ መንግስት ማፍለስ ነው፡፡


አስተያየት ለመፃፍ