Saturday, December 27, 2014

የሲኦል ነገር- Is Hell for real?




ፊልሙን ካየሁት ትንሽ ቆይቷል፤ ካልተሳሳትኩ የፊልሙ ርእስ ‹‹ ቀሚስ የለበስኩለት›› የሚል ነበር፡፡ በእውነቱ ፊልሙ አይቼ በጣም ከወደድኳቸው ጥቂት ፊልሞች መካከል አንዱ ነው፡፡ ጥርት ምጥን ተደርጎ የተሰራ ምርጥ ፊልም ነው፡፡ ሆኖም ግን ለዚህች ፅሁፍ መነሻ የሆነኝን ሰይጣናዊ አስተሳሰብም ያስተዋልኩት በዚህ ፊልም ውስጥ ነው፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡- በፊልሙ ውስጥ ያሉት ዋና ገጸ-ባህሪያት(የገጸ-ባህሪ ስማቸውን አላስታውስም) ዘሪቱ እና ዲበኩሉ በሚነጋገሩት አንድ ክፍል ውስጥ ገሃነም እውነት እንዳልሆነ ማለትም ውሸት እንደሆነ እንደሚያስብ ይናገራል ይህንንም ልጅ ሆነን ከሚነገረን የአዉ ታሪክ ጋር ያመሳስለዋል፡፡ የአዉ ታሪክ ማለት አንድ ህፃን ልጅ ጨዋ ልጅ እንዲሆንና ታዛዥ እንዲሆን ቤተሰቦቻችን ዋ! አዉን እጠራልሃሉ፣ አዉ ይመጣልሃ፣ አዉ ይቆጣል… የመሳሰሉትን በማለት ያስፈራሩን የነበረውን ማለቱ ነው፡፡ ይህንንም የሚያደርጉት እኛን ለመጉዳት ወይም ፈሪ ለማድረግ ሳይሆን ታዛዥና ጨዋ ልጆች እንድንሆን በማሰብ ነው (ግን የዚህ ዘመን ልጆች አዉን ይፈራሉ?  እኔንጃ)፡፡ የሆነው ሆኖ ዲበኩሉ ማለት የፈለገው ልክ እንደ አዉ ታሪክ ሁሉ አምላክም ጥሩ ሰዎች እንድንሆን በማሰብ የሌለውን የገሃነም ታሪክን ፈጥሮ እያስፈራራን እንደሚያኖረን ይህም ለኛ በማሰብ እንደሆነ ነው፡፡ ትልቁ ጥያቄ ታዲያ ይሄ ነው፡፡ እውነት ገሃነም የፈጠራ ታሪክ ነው? በእግዚአብሔር ሃሳብና መንገድ ብንሄድም ባንሄድም መጨረሻችን ያው ተመሳሳይ ነው? ካልሆነስ እውነቱ ምንድነው? በዚህች አጭር ፅሁፍ ስለዚህ ጉዳይ ባጭሩ ለማብራራት እሞክራለሁ፣ በጥሞና አንብቡልኝ የተሰማችሁን አስተያየትም ፃፉልኝ፡፡



ይህን ፅሁፍ መፃፍ ከጀመርኩ በጣም ረጅም ጊዜ አልፎኛል፡፡ እስካሁንም ፅሁፉን ሳልጨርሰው የቆየሁባቸው ሁለት ዋና ዋና ምክኒያቶች ናቸው፡፡ የመጀመሪያው የራሴ ስንፍና ነው፡፡ ሁለተኛውና መሰረታዊ የሆነው ምክኒያት ግን ጉዳዩ ያሰብኩትን ያህል ቀላልና ግልፅ አለመሆኑን በመረዳቴ ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ለመፃፍ አስቤ የተለያዩ ፅሁፎችን ሳሰባስብና የተለያዩ ድረ-ገፆችን ስመለከት ትልልቅ የሚባሉ አግልጋዮችና የቤተክርስቲያን መሪዎች ጭምር በጉዳዩ ላይ ምን ያህል የተለያየ አመለካከት እንዳላቸው ለመገንዘብ ችያለሁ፡፡ ስለዚህ ጉዳዩን በጥልቀት ለመዳሰስ ከመሞከር ይልቅ መሰረታዊ የሆነውን የመፅሃፍ ቅዱስ ሃሳብ ማስቀመጡን መርጫለሁ፡፡ ለመንደርደሪያ ያህል ግን የተወሰኑ ሰዎችን አመለካከት በቅድሚያ ላቅርብ፡-
ሊቃነ ጳጰስ ቤነዲክት፡- በመፅሃፍ የተፃፈው እሳት ተምሳሌታዊ ሳይሆን እውነተኛ እሳት ነው አርሱም ለዘላለም የማይጠፋ ነው
ሊቃነ ጳጳስ ጆን ፖል፡- ገነት ማለት የሚታይ ወይም የሚዳሰስ ቦታ ወይም አብሰትራክት ነገር አይደለም፤ ነገር ግን ከአምላክ ጋር በሙላት ህብረት ማድረግ ማለት ነው፡፡ በተመሳሳይም ገሀነምም የሆነ ቦታ ሳይሆን በሀጢያት ምክኒያት ከአምላክ መነጠል ወይም መራቅ ነው፡፡ በአጠቃላይ ተምሳሌታዊ ነገር ነው፡፡
ቢሊግርሃም፡-  ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ገሀነም እሳት ሲናገር የተናገረው ምሳሌአዊ ስለሆነው እሳት ነው እንጂ ስለ አእውነተኛ እሳት አይደለም፡፡ እሳት የሚለው ምሳሌ ምናልባትም የሚወክለው እነደ እሳት የሚያቃጥል አምላክነ መፈለግና መጠማት ሲሆን ነገር ግን አምላክን አለማግኝት ነው፡፡
ከላይ ያየናቸው ሰዎች አመለካከት ጉዳዩ ምን ያህል አወዛጋቢ መሆኑን እንረዳለን፡፡ በመቀጠል ዋና ዋና የሚባሉት አመለካከቶችን ለማየት እንሞክር፡፡
የመጀመሪያው አመለካከት ፍፁም መካድ ነው፡፡ ይኽውም ገሀነም የሚባል ነገር የለም የሚል እምነትና አመለካከት ነው፡፡ ይህ አመለካከት ገሀነም ቤ/ክርስቲያን ሰዎችን በማስፈራራት ፍላጎቷን ለማስፈፀም የምትጠቀምበት የፈጠራ ታሪክ ነው ይላል፡፡ ይህ አመለካከት በእውነተኛ ታሪክ ላይ ተመስርቶ በተሰራው Heaven is for real በተሰኝው ምረጥ የ2014 ፊልም ላይ በጥሩ መንገድ ተገልል ተመልከቱት፡፡
ሁለተኛው አመለካከት ደግሞ ገሃነም በምድር ያለ ስቃይ ነው ብሎ ያምናል፡፡ የህም ማለት ገሃነም ማለት በምድር ሳለን በህይወታችን የሚያልፉ መጥፎና ክፉ ነገሮች በሙሉ ማለት ነው፡፡ ሶስተኛው አመለካከት ደግሞ ( Annihiiationism) ተብሎ የሚጠራው ሲሆን ገሃነም በስተመጨረሻ የሁሉም መጥፎ ሰዎች ድምጥማጣቸው መጥፋትን ያመለክታል ብለው ያምናሉ፡፡
አራተኛው አመላካከት ደግሞ በመታደስ የሚያምኑ ሲሆን በስተመጨረሻ ሁሉም ሰው ይድናል ብለው ያምናሉ፡፡ አምስተኛው አመለካከት ደግሞ ገሃነም በትክክልም የሚገኝ ቦታ ነው ስቃዩም ዘላለማዊና የማያቋርጥ ነው ይላል፡፡
ይህን ሁሉ ከተመለከትን እውነት ገሃነም ወይም ሲኦል የሚባል ነገር አለን? መፅሃፍ ቅዱስስ ስለዚህ ጉዳይ ምን ይለናል?
የእብራይስጡ ሼኦል የሚለው ቃል በብሉይ ከዳን ከ65 ጊዜ በላይ ተጠቅሷል፡፡ ይህ ቃልም ገሃነም፣ ሞት፣ ጥፋት መቃብር እና ጥፋት ተብሎ በሌሎች ቋንቋዎች ተተርጉሟል፡፡
ለምሳሌ ያህል
መዝ 49፡13-14
ይህች መንገዳቸው መሰናክላቸው ናት፥ ከእነርሱም በኋላ የሚመጡ በአፋቸው እሺ ይላሉ።

እንደ በጎች ወደ ሲኦል የሚሄዱ ናቸው፥ እረኛቸውም ሞት ነው ቅኖችንም በማለዳ ይገዙአቸዋል፥ ውበታቸውም ከመኖሪያቸው ተለይታ በሲኦል ታረጃለች።

በአዲስ ኪዳንም በግሪክ ሃዴስ እና ገሂና የሚባሉ ቃለት ጥቅም ላይ ውለዋል፡፡ ለምሳሌ ያህልም ሐዋ 2፡27-31 እና ማቴ 25፡41 ላይ ማስተዋል ይቻላል፡፡
በአማርኛችንም በብሉይ ኪዳን በዋናነት ሲኦል የሚለው ቃል በጥቅም ላይ የዋለ ሲሆን (58 ጊዜ) በአዲስ ኪዳን ደሞ ገሀነም 11 ጊዜ ሲኦል ደግሞ 10 ጊዜ ተፅፎ እናገኛለን፡፡
በአጭሩ ሲኦል ወይም ገሀነም መፅሃፍ ቅዱስ ውስጥ የሌለ ሃሳብ አይደለም ማለት ነው፡፡ እሺ! መፅሃፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኝ ሃሳብ ከሆነ፣ በመፅሃፍ ቅዱስ ውስጥ በምን አይነት ሁኔታ ነው የተጠቀሰው የሚለውን ደግሞ ቀጥለን እንመልከት፡፡
1.  በገሃነም ያለው ቅጣት ዘላለማዊ ነው ( የማይቋረጠጥ ቅጣት)
ኢሳያስ 66 ፡ ወጥተውም በእኔ ያመፁብኝን ሰዎች ሬሳቸውን ያያሉ ትላቸው አይሞትምና፥ እሳታቸውም አይጠፋምና ለሥጋ ለባሽም ሁሉ አስጸያፊ ነገር ይሆናሉ።
2
ዳንኤል 12፡ በምድርም ትቢያ ውስጥ ካንቀላፉቱ ብዙዎች ይነቃሉ እኵሌቶቹ ወደ ዘላለም ሕይወት፥ እኵሌቶቹም ወደ እፍረትና ወደ ዘላለም ጕስቍልና።
ማቴዎስ 25፡ እነዚያም ወደ ዘላለም ቅጣት፥ ጻድቃን ግን ወደ ዘላለም ሕይወት ይሄዳሉ።
ራዕይ ዮሐንስ 14፡ የሥቃያቸውም ጢስ ለዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ይወጣል፥ ለአውሬውና ለምስሉም የሚሰግዱ የስሙንም ምልክት የሚቀበል ሁሉ ቀንና ሌሊት ዕረፍት የላቸውም።
-    መፅሃፍ ቅዱሳችን በግልፅ እንደሚያስተምረን በሲኦል ያለው ጥፋት፣ ቅጣትና ስቃይ ለዘለአለም መሆኑን በግልፅ መረዳት እንችላለን፡፡
2.  ገሀነም ከእግዚአብሔር ህብረት መጉደል ነው
2ተሰ 1፡ 9-10
በዚያም ቀን በቅዱሳኑ ሊከብር፥ ምስክርነታችንንም አምናችኋልና በሚያምኑት ሁሉ ዘንድ ሊገረም ሲመጣ፥ ከጌታ ፊት ከኃይሉም ክብር ርቀው በዘላለም ጥፋት ይቀጣሉ።
-    ከእግዚአብሄር ህብረት መራቅ ምን አይነት አሰቃቂ ነገር ሊሆን እንደሚችል ከመገመት ውጪ ደፍሮ መናገር በጣም ከባድ ይመስላል፡፡ ስለዚህ መፅሃፍ ቅዱስ ስለሲኦል የሚነግረን ሌላ ቁምነገር ከጌታ ጋር ህብረት ማድረግ አለመቻል ነው፡፡
3.  ገሃነም በእሳት መቃጠያ እና መሰቃያ ስፍራ ነው
ማቴ 1341
የሰው ልጅ መላእክቱን ይልካል፥ ከመንግሥቱም እንቅፋትን ሁሉ ዓመፃንም የሚያደርጉትን ይለቅማሉ፥
ወደ እቶነ እሳትም ይጥሉአቸዋል፤ በዚያ ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል።
ራዕይ 20፡ 15
በሕይወትም መጽሐፍ ተጽፎ ያልተገኘው ማንኛውም በእሳት ባሕር ውስጥ ተጣለ።
-    ከላይ የጠቀስኳቸውን ጨምሮ ብዙ የመፅሃፍ ቅዱስ ጥቅሶች በስተመጨረሻ እግዚአብሔር ሃጢያተኞችን በእሳት እንደሚቀጣ እና እሳቱም ለዘለአለም የማይጠፋ መሆኑን ይነግሩናል፡፡
4.  ሲኦል ለአመፀኞች፣ ለሃጢያተኖች፣ ለሰይጣ እና ለሃሰተኛው ነብይ ነው
መዝ 917
ኃጢአተኞች ወደ ሲኦል ይመለሳሉ፥ እግዚአብሔርን የሚረሱ አሕዛብም ሁሉ።
18

ማቴዎስ25፡  41
በዚያን ጊዜ በግራው ያሉትን ደግሞ ይላቸዋል። እናንተ ርጉማን፥ ለሰይጣንና ለመላእክቱ ወደ ተዘጋጀ ወደ ዘላለም እሳት ከእኔ ሂዱ።
ራዕይ 20፡ 10
ያሳታቸውም ዲያብሎስ አውሬውና ሐሰተኛው ነቢይ ወዳሉበት ወደ እሳቱና ወደ ዲኑ ባሕር ተጣለ፥ ለዘላለምም እስከ ዘላለም ቀንና ሌሊት ይሣቀያሉ።




በእውነቱ ከሆነ ከላይ ያየናቸውን ጥቅሶች የተመለከተ ማንም ሰው ሲኦል ወይም ገሃነም የሚባለ ነገር የለም ብሎ ለማመን የሚያስችል ምክንያት አያገኝም፡፡ ሲኦል ወይም ገሃነም የምንቀልድበት ወይም የምናሾፍበትም ጉዳይ እንዳልሆነ ማስተዋል እንችላለን፡፡
ይህን ጉዳይ አስመልክቶ የሚነሳው መሰረታዊ ጥያቄ
 "እጅግ አፍቃሪና ሰዎችን ወዳድ የሆነው ፈጣሪ እንዴት ሰዎችን ለዘለአለም በሲኦል ይቀጣል?" የሚል ነው፡፡ አውነትም ትክክል እኮ ነው፤ ምን ሲደረግ? የሚያስብል ጥያቄ ነው፡፡ ይህ ጥያቄ ግን "እንዴት አንድ ደግ እና ሩህሩህ ዳኛ ነፍሰ ገዳይ ወንጀለኛን ለእድሜ ልክ ፍርድ ወደ እስር ቤት ይልካል?"ብሎ የመጠየቅ አይነት ቀሽም ጥያቄ ነው፡፡እግዚአብሔር ሉአላዊና የፍትህ አምላክ መሆኑንም መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ ግን እግዚአብሄር የመዳኛውን መንገድ ማዘጋጀቱንም ማወቅ ይኖርብናል፡፡ ሰዎች ወደዚህ ስፍራ እንዳይሄዱ ይህን እውነት መናገር ደግሞ ከእኛ ይጠበቃል፡፡
ታዲያ ወደዚህ አስጨናቂና አስፈሪ ቦታ እንዳንሄድ ምን እናድርግ? ይህነው መጠየቅ ያለበት መሰረታዊ ጥያቄ፡፡ መልሱም በጣም አጭርና ግልፅነው፡- ከዚህ አስጨናቂ ስቃይ ማምለጥ ይቻላል፣ ሰዎች ከዚህ ስቃይ እንዲያመልጡም የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው፡፡
ነገር ግን መዳን የሚቻለው እንዴት ነው? በመጀመሪያ የሠው ዘር በሙሉ ሃጢያተኛ መሆኑን ማወቅ አለበት፡፡ ሰው ለመዳን መጀመሪያ ማድረግ ያለበትም ይህንኑ ነው፡፡ "ሐጢያተኛ ነኝ"፣ "መልካምነት የለኝም"፣ "ለመዳን ብቁ የሚያደርገኝ ምንም መልካምነት ወይም ፅድቅ ስለሌለኝ የሚያድነኝ ወይም የሚረዳኝ ያስፈልገኛል" በማለት ሰው ሃጢያተኝነቱን ማመን ይገባዋል፡፡ ቀጣዩ ጉዳይ ታዲያ ከዚህ ሃጢያተኝነትና ሊመጣ ካለው ጥፋት በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን ብቻ መዳንና ከጥፋት ማምለጥ እንደሚቻል ማመን ነው፡፡ በኢየሱስ ክርስቶስ ማመን ማለት ታዲያ ምንድን ነው? በኢየሱስ ክርስቶስ ማመን ማለት ኢየሱስ ክርስቶስ፡- አምላክ ሆኖ ሳለ የሰው ልጆችን ለማዳን እራሱን ዝቅ በማድረግ በሰው አምሳል ስለመገኝቱና ሰው ስለመሆኑ፣ በሰውነቱም በሰው ልጆች ፋንታ ሆኖ ስለ ሰው ዘር ሁሉ ሀጢያት በመስቀል ተሰቅሎ ስለመሞቱ፣ ሞቶም ስለ መቀበሩ ፣ ተቀብሮም በሶስተኛው ቀን ከሞት ስለመነሳቱና ወደ ሰማይ ስለማረጉ.፣ ወደ ሰማይ ማረጉም ብቻ ሳይሆን ተመልሶ እንደሚመጣም ተስፋ መስጠቱን ማመን ማለት ነው፡፡ ይህን በማመን ማንነትንም ለጌታ አሳልፎ በመስጠት አውነተኛ የዳነ ክርሰቲያን መሆን ይቻላል በዚህም ከዘላለም ሞትና ስቃይ ማምለጥ ይቻላል፡፡ እግዚአብሔርም ለሰው ልጆች ሁሉ ያዘጋጀው ብቸኛ፤ ልድገመው ብቸኛ የመዳን መንገድ ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን ማመን ያስፈልጋል፡፡
ለማጠቃለያ ያህል በመግቢያዬ ያነሳሁትን ጥያቄዎች በአጭር በአጭሩ ለመመለስ ልሞክር፡፡ እግዚአብሔር እንድንኖርበት በሚፈልገውና በሚወደው የፅድቅ መንገድ ብንሄደም ባንሄድም መጨረሻችን ተመሳሳይ ነውን? በፍፁም አይደለም ምክኒያቱም እግዚአብሔር ሃጢያተኞችን እንደሚቀጣ በተደጋጋሚ በቃሉ ተመልክተናልና፡፡ ገሃነም ወይም ሲኦል እንዳለ ሁሉ ገነት እንዳለም ማስተዋል ይኖርብናል፡፡ በክርስቶስ ኢየሱስ አምነው በፅድቅ ህይወት የሚኖሩ ሁሉ በስተመጨረሻ ያከበሩት ጌታ ለዘለአለም ያከብራቸዋል፡፡ በፅድቅ መኖር ከጌታ ሽልማትን ያስገኛል፡፡
አውነት ነው ይህ የምለው የመዳኛ መንገድ ለብዙ ሰዎች ትርጉም የማይሰጥ ሞኝነት ይመስላል ነገር ግን ከዚህ ሌላ የመዳኛ መንገድ የለም፡፡
1 ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች
123 
እኛ ግን የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን፤ ይህም ለአይሁድ ማሰናከያ ለአሕዛብም ሞኝነት ነው፥

ሩክማን Peter Ruckman የተባሉት ፀሃፊ " የገሃነምን ጉዳይ ሊያቀዘቅዙ የሚፈልጉ ሰዎች ቀጥታ ወደ ገሃነም የሚሄዱ ሰዎች ናቸው" ብለዋል፡፡ እውነት ነው፤ ጓደኞቼ አትሳሳቱ እውነትን የሚሸፋፍን ክፉ ዲያብሎስ ነው አላማውም በመጨረሻ ቀን ሰዎችን ሁሉ ከራሱ ጋር ወደ ዘላለም ጥፋት ይዞ መሄድ ነው፡፡ ስለዚህ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን እውነተኛ ክርስቲያናዊ የቅድስና ህይወትን በመኖር ከዘላለም ጥፋት እናምልጥ የምንወዳቸው ሰዎችንም ይህን እውነት በማስረዳት ከዘላለም ሞት እንታደጋቸው፡፡
By :Yosef M.