Saturday, May 9, 2015

እውነት እግዚአብሔር አለን? ክፍል ሁለት



ክፍል ሁለት - በእውነትም እግዚአብሔር አለ!
ባለፈው ፁሁፌ በምድራችን ላይ ከምናያቸው መልካም ያልሆኑ ነገሮች የተነሳ የአምላክ መኖርን እንዴት ልንጠይቅ እንደምንችል ዋና ዋና የሆኑ አራት ነጥቦችን በማንሳት ለማሳየት ሞክሬ ነበር፡፡ በዚህ ፅሁፌ ደግሞ ለነዚህ ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት እሞክራለሁ አንብባችሁ የተሰማችሁን አስተያየት ስጡኝ፡፡ ስለምታነቡልኝም አመሰግናለሁ፡፡
1.  በውድቀት ውስጥ ያለች አለም
ስለዚህ ጉዳይ ለመፃፍ አስቤ የተለያዩ ፅሁፎችን ማሰባሰብና ማንበብ ከጀመርኩ ምናልባትም ከሶስት ወር በላይ ሳይሆነኝ አይቀርም፡፡ እጅግ በሚደንቅ ሁኔታ ያስተዋልኩት ነገር ቢኖር በምድር ውስጥ ያለው ክፋት መንስኤ በውድቀት ውስጥ ባለች ምድር ላይ መኖራችን መሆኑን ብዙ ፀሃፊያን ማብራራት አለመፈለጋቸው ነው፡፡ መፅሃፍ ቅዱሳችን ግን የሚነግረን ይህንን ነው፡፡
ዘፍ 2፡8 እግዚአብሔር አምላክም በምሥራቅ በዔድን ገነትን ተከለ የፈጠረውንም ሰው ከዚያው አኖረው።
እግዚአብሔር በቅድሚያ ለሰው የሚያስፈልገውን በሙሉ ካሟላና ካስተከከለ በኋላ ለሰው እጅግ መልካም በሆነው ቦታ ሰውን አስቀመጠው፣ ሃላፊነትም ሰጠው፡፡ ብዙም ሳይቆይ ግን በዘፍ 3 ይህ መልካሙ ነገር ሁሉ የተመቻቸለት ሰው የአምላኩን ትእዛዝ ሲጥስ እንመለከተዋለን፡፡ በዚህም ምክንያት እራሱን ጨምሮ ምድርም ለእርግማን ተዳርጋለች፡፡
ዘፍ 3፡17 አዳምንም አለው። የሚስትህን ቃል ሰምተሃልና፥ ከእርሱ እንዳትበላ ካዘዝሁህ ዛፍም በልተሃልና ምድር ከአንተ የተነሣ የተረገመች ትሁን በሕይወት ዘመንህም ሁሉ በድካም ከእርስዋ ትበላለህ…
አምላክ ሰውን ሲፈጥረው ነፃ ፍቃድ ያለው ፍጡር አድርጎ ነው የፈጠረው፡፡ ሰው ይህን ነፃ ፍቃዱን ለመልካምም ለክፉም አመዛዝኖ መጠቀም የሚችል ፍጡር ነው፡፡ ሰው ይህን ነፃ ፍቃዱንና የማመዛዘን ችሎታውን ከእግዚአብሔር ፍቃድ በተቃራኒ ለመሄድ ተጠቀመበት፡፡ ከዚህ የተነሳም እራሱን ጨምሮ ምድርንም ለእርግማን አበቃት፡፡
በምድር የሚሆኑ ክፉ ነገሮች ሁሉ ከሁለት ዋና ዋና ምንጮች ይፈልቃሉ፡፡ የመጀመሪያው ከሰው ክፋት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ከተፈጥሮ ነው፡፡ ጦርነት፣ እርስ በእርስ መጠፋፋት እና መከፋፋት፣ ሰዎች ሰዎችን መጉዳት የመሳሰሉት ሁሉ ከተረገመው ሰው ክፉ ልብ የሚመነጩ ናቸው፡፡ የምድር መናወጥ፣ ድርቅ፣ ረሃብ እና የመሳሰሉት ደግሞ ከተረገመችው ምድር የሚመነጩ ናቸው፡፡
2.  ኢየሱስ ክርስቶስም ይህ እንደሚሆን አስቀድሞ ነግሮናል
ሌላው ማስተዋል ያለብን መሰረታዊ ጉዳይ ኢየሱስ ክርስቶስ የምድራዊ ተድላን ተስፋ እንዳልሰጠን ነው፡፡ ዮሐ 16፡33 በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ በማለት በምድር ስንንኖር በመከራ ውስጥ መኖር የማይቀር የህይወት ፈተና መሆኑን ኢየሱስ ክርስቶስ ቃል በቃል ነግሮናል ስለዚህም በህይወታችን የተለያዩ መከራዎች ማለፋቸው የእግዚአብሔር አለመኖር ማስረጃ አይደለም፡፡
  1. ኢየሱስ እራሱ በስቃይና በችግር ውስጥ አልፏል
መፅሃፍ ቅዱስ እንደሚነግረን ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ ነው፡፡ ሉቃ3፡38 የእግዚአብሔር ልጅ። ይለናል ነገር ግን ምንም ያህል ፃድቅና ነውር የሌለበት ቢሆንም የምድርን ስቃይና ችግር መጋፈጥ ግን አልቀረለትም፡፡ በምድር ሲመላለስ እንደ ሰው ስለ መፈተኑ ቅዱስ ቃሉ ይነግረናል፡፡ ዕብ 4፡15 ከኃጢአት በቀር በነገር ሁሉ እንደ እኛ የተፈተነ ነው እንጂ...
ይህ ፈተና በመስቀል ላይ እጅግ አሰቃቂ በሆነ ህመምና ስቃይ አጣጥሮ እስከ መሞት የደረሰ ስቃይ ነው፡፡ ኢየሡስ ይህን ሁሉ ስቃይ የተሸከመው አምላክ ስላልነበረ ግን አይደለም፡፡ በዚህ ስቃይ ውስጥ አምላክ እንዲያልፍ ስለፈቀደ እንጂ፡፡
  1. የእምነት አባቶች ምስክርነት
ዕብ 11፡36-38
ሌሎችም መዘበቻ በመሆንና በመገረፍ ከዚህም በላይ በእስራትና በወኅኒ ተፈተኑ፤
በድንጋይ ተወግረው ሞቱ፥ ተፈተኑ፥ በመጋዝ ተሰነጠቁ፥ በሰይፍ ተገድለው ሞቱ፥ ሁሉን እያጡ መከራን እየተቀበሉ እየተጨነቁ የበግና የፍየል ሌጦ ለብሰው ዞሩ፤
ዓለም አልተገባቸውምና በምድረ በዳና በተራራ፥ በዋሻና በምድር ጕድጓድ ተቅበዘበዙ።
የእብራውያን ፀሃፊ የሚዘረዝራቸው የእምነት አባቶች እግዚአብሔር ተስፋን የሰጣቸው ፃድቅና የእምነት ሰዎች ናቸው፡፡ ነገር ግን ምንም ያህል ታላቅ የተስፋ ቃል የተሰጣቸው ሰዎች ቢሆንም በምድር ከመቅበዝበዝ፣ መከራን ከመቀበልና ከመንከራተት ግን አላመለጡም፡፡ ይህ በህይወታቸው ያለፈው መከራና ስደት ግን እግዚአብሔር አምላክ የለም እንዲሉ አላደረጋቸውም፡፡
  1. እግዚአብሔር በአላማ ክፋትን ይፈቅዳል
እግዚአብሔር አምላክ ሁል ጊዜም ባይሆን ክፉ ነገርን አንድ አንድ ጊዜ ወደ እኛ ሊያመጣ ይችላል፡፡
  1. ለቅጣት ፡- በብሉይ ኪዳንም ሆነ በአዲስ ኪዳን እግዚአብሔር ሰዎችን በሓጢያታቸው ምክንያት ሲቀጣና ሲቀስፍ እንመለከተታለን፡፡(ዘፍ6 ጎርፍ፣ ዘፍ 18-19 የሰዶም ጥፋት፣ ዘፀ 7-12፣ ሐዋ 12፡19-23፣ 2ጴጥ 2፡9-10፣ 1ቆሮ 11፡27-32) ይህ ማለት ግን የሚደርስብን ችግርና መከራ በሙሉ የእግዚአብሔር ቁጣና መቅሰፍት ነው ማለት አይደለም፡፡
  2. ሰዎች ወደ ንስሃ እነስኪመለሱ ይታገሳል፡- በተለይ የሞራል ውድቀትን እና የማህበራዊ ኢ-ፍትሃዊነትን እግዚአብሔር ለምን ይታገሳል ለሚለው ጥያቄ ሐዋሪያው ጴጥሮስ በሁለተኛው መልእክቱ እንዲህ በማለት ምላሽ ይሰጣል 1ጴጥ 3፡9 ለአንዳንዶች የሚዘገይ እንደሚመስላቸው ጌታ ስለ ተስፋ ቃሉ አይዘገይም፥ ነገር ግን ሁሉ ወደ ንስሐ እንዲደርሱ እንጂ ማንም እንዳይጠፋ ወዶ ስለ እናንተ ይታገሣል።
  3. ወደ ራሱ ሊያስጠጋን፡-  በመከራ በመፅናትና ወደ አምላኩ በመጠጋት ጳውሎስን የመሰለ ምስክር በመፅሃፍ ቅዱሳችን ያለን አይመስለኝም፡፡ ለቆሮንጦስ ሰዎች በፃፈው መልእክት ይህን ብሏል (2ቆሮ 1፡8-9)፡-
በእስያ ስለ ደረሰብን መከራችን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ታውቁ ዘንድ እንወዳለንና፤ ስለ ሕይወታችን እንኳ ተስፋ እስክንቆርጥ ድረስ ከዓቅማችን በላይ ያለ ልክ ከብዶብን ነበር፤
አዎን፥ ሙታንን በሚያነሣ በእግዚአብሔር እንጂ በራሳችን እንዳንታመን፥ እኛ ራሳችን የሞትን ፍርድ በውስጣችን ሰምተን ነበር።
በሌላ ቦታ ደግሞ በስጋው ስለነበረ ህመም ሲናገር እንዲህ ብሏል(2ቆሮ 12፡9)
9
እርሱም፦ ጸጋዬ ይበቃሃል፥ ኃይሌ በድካም ይፈጸማልና አለኝ። እንግዲህ የክርስቶስ ኃይል ያድርብኝ ዘንድ በብዙ ደስታ በድካሜ ልመካ እወዳለሁ።
ስለዚህ ከጳውሎስ መልእክቶች የምንረዳው እግዚአብሔር ወደ እርሱ ይበልጥ እንድንጠጋ አንዳንድ ችግሮችን ሊፈቅድ እንደሚችል ነው፡፡
  1. እኛን ለማስተማር፡- ሮሜ 5፡3-4 ይህም ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን መከራ ትዕግሥትን እንዲያደርግ፥ ትዕግሥትም ፈተናን ፈተናም ተስፋን እንዲያደርግ እያወቅን፥ በመከራችን ደግሞ እንመካለን፤
ይህ በተለይ አምላክ እኛ ፍፁማን እንድንሆን ካለው ፍላጎት የተነሳ በተለያዩ መከራዎች ውስጥ እንድናልፍ ስለመፍቀዱ ያስረዳል፡፡ ያዕ 1፤2-4 ወንድሞቼ ሆይ፥ የእምነታችሁ መፈተን ትዕግሥትን እንዲያደርግላችሁ አውቃችሁ፥ ልዩ ልዩ ፈተና ሲደርስባችሁ እንደ ሙሉ ደስታ ቍጠሩት ትዕግሥትም ምንም የሚጎድላችሁ ሳይኖር ፍጹማንና ምሉዓን ትሆኑ ዘንድ ሥራውን ይፈጽም።
  1. ህብረታችን እንዲጠነክር፡- መፅሃፍ ቅዱስ ክርስቲያናዊ ህብረትን በተመለከተ በጣም ትልቅ ትኩረት ይሰጣል፡፡ አንዱ መፅሃፍ ቅዱስ የሚያሳየን ጉዳይ በመከራ ህብረታችን መጠንከር እንደሚኖርበት ነው፡፡ 2 ቆሮ 1፡3-4፣ ገላ 6፡2፣ ሮሜ 12፡15...
ታዋቂው ፀሃፊ ሲ.ኤስ ሊዊስ ይህን ብሏል “God whispers to us in our pleasures, speaks in our conscience, but shouts in our pains: it is His megaphone to rouse a deaf world.” እስካሁን በጠቃቀስኳቸው ነጥቦች ምናልባትም መከራ በእግዚአብሔር ፈቃድ ሊሆን እንደሚችል ነው፡፡ በተለይ ደግሞ ከእርሱ ጋር ያለንን ህብረት ለማጠንከር መከራና ችግር በህይወታችን ሊያልፍ ይችላል፡፡ ሁሉም ችግርና ስቃይ ግን በዚህ ምክንያት ነው ማለት አይደለም፡፡

  1. እዮብ
ብዙዎቻችን ስለ እዮብ ስናስብ የእዮብ ስቃይና መከራ እንዲሁም ታጋሽነቱ በቅድሚያ ወደ አእምሯችን የሚመጡ ሃሳቦች ናቸው፡፡ ነገር ግን የእዮብን መፅሃፍ በጥንቃቄ ከመረመርነው ከዚህ የበለጠ ሌላ ትልቅ መልእክት አለው፡፡ እኔም ለዚህ ˝እውን እግዚአብሔር አለን?˝ ለሚለው ጥያቄ ባይጥምም ልብን የሚሞላ ምላሽ የምለው ይህንኑ የእዮብ መፅሃፍ መልእክትን ነው፡፡
የእዮብ መፅሃፍ ሲጀምር እዮብን በማስተዋወቅ ይጀምራል፡፡ ስለ ሃብቱ፣ስለ ቤተሰቡ እና ስለ ቅድስናው ይነግረናል፡፡ ከዚያ በመቀጠል ሰይጣን እና እግዚአብሔር ያደረጉትን ውይይት እናነባለን፡፡ ወዲያውም እዮብ ሁሉ ነገሩን ሲያጣ፡፡ ሁሉ ነገሩን ካጣ በኋላ ይህ አልበቃ ብሎ ጤንነቱም ይጨመርበታል፡፡ በሁለት ምእራፎች እዮብ በጣም ከተከበረ ሃብታም ሰውነት በአንድ ጊዜ ወደ ድሃ ምስኪን ሰውነት ይለወጣል፡፡ የመፅሃፉን እረጅም ክፍል የያዘው እዮብ ከወዳጆቹ ጋር ያደረገው ንግግርና ምልልስ ነው፡፡ በመጨረሻ እግዚአብሔር ራሱ ይመጣና ከእዮብ ጋር ይነጋገራል፡፡
 እዮብ በዚህ ሁሉ መከራና ስቃይ ውስጥ ሲያልፍ እግዚአብሔር እና ሰይጣን ስለተነጋገሩት ነገር የሚያውቀው ታሪክ የለም፡፡ እዮብ ልጆቹ እና ሃብቱ በሙሉ ሲወድም እግዚአብሔር እና ሰይጣን ስለተነጋገሩት ነገር የሚያውቀው ታሪክ የለም፡፡ እዮብ ገላው በቁስል ሲመታ እግዚአብሔር እና ሰይጣን ስለተነጋገሩት ነገር የሚያውቀው ታሪክ የለም፡፡ እዮብ ወዳጆቹ ስለወረደበት መአት የመሰላቸውን አስተያየት ሲሰጡ እግዚአብሔር እና ሰይጣን ስለተነጋገሩት ነገር የሚያውቀው ታሪክ የለም፡፡ ሚስቱ አምላክን ሰድበህ ሙት ብላ ስትመክረው እግዚአብሔር እና ሰይጣን ስለተነጋገሩት ነገር የሚያውቀው ታሪክ የለም፡፡ በህይወቱ በእውነት እጅግ አስከፊና አስቸጋሪ ጊዜን አሳልፏል፡፡
በስተመጨረሻ እራሱ እግዚአብሔር ተገለጠለት፡፡ ተገልጦለት ግን በእዮብ ህይወት የሆነው ሁሉ ለምን እንደሆነ አላበራራለትም፡፡ "እዮብ እኔ እና ሴጣን ስለአንተ ተነጋግረን ነበር፡፡ ሰይጣን በአንተ ላይ ያለውን ጥበቃዮን ባነሳ የምትሰድበኝ መሰሎት ነበር፡፡" ብሎ እግዚአብሐር ለእዮብ ማብራሪያ አልሰጠም፡፡ የሆነው ነገር እጅግ አስደናቂ ነበር፤ "እስኪ ልጠይቅልህ መልስልኝ" ነበር ያለው፡፡ከምእራፍ 38 እስከ 41 እግዚአብሔር እንዴት ያለ ታላቅና ሉአላዊ አምላክ እንደሆነ ለእዮብ በጥያቄ አሳየው፡፡ ይቅርና የሚታየው ታላላቅ ነገር ቀርቶ በጣም ጥቃቅን ነገሮች ሁሉ በእርሱ አውቅና እንደሚሆኑ አሳየው፡፡ እግዚአብሔር አምላክ በሁሉ ነገር አዋቂ እና ትክክክ እንደሆነ አስረዳው፡፡ አምላክ ሁሉን የሚቆጣጠርና ሁሉን የሚያውቅ እንደሆነ አሳየው፡፡ በነዚህ አራት ምእራፎች እዮብ መናገር የቻለው አንድ ነገር ብቻ ነው፡- እነሆ፥ እኔ ወራዳ ሰው ነኝ የምመልስልህ ምንድር ነው? እጄን በአፌ ላይ እጭናለሁ። አንድ ጊዜ ተናገርሁ፥ አልመልስምም ሁለተኛ ጊዜም፥ ከእንግዲህ ወዲህ አልናገርም።
የእግዚአብሔር ታላቅነትና አምላክነት ሊመልሰውና ሊያስተውለው ከሚችለው ሁሉ በላይ ነው እና ምንም መናገር አልቻለም፡፡ ስለዚህም ዝም አለ፡፡
ስለዚህ የእዮብ መፅሃፍ ቁልፍ መልእክት ይህ ነው፡፡ እግዚአብሔር በነገር ሁሉ አዋቂ እና ትከክክል ነው፡፡ እግዚአብሔር ፍፁም ሉአላዊ አምላክ ነው፡፡ ምንም እንኳን ሰዎቸ በጣም አሰቃቂ መከራ እና ችግር ውስጥ ቢያልፉም፣ ምንም እነኳን መከራ በላያችን ቢፈራረቅም፣ ለምን በመከራ እና በስቃይ ወስጥ እንደምናልፍ ቢገባንም ባይገባንም እግዚአብሔር አምላክ ሊፈራ ሊከበር እና ሊመለክ የሚገባው ብቸኛ አመላክ ነው፡፡ እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ጠየቀው
8
በውኑ ፍርዴን ታፈርሳለህን? አንተስ ጻድቅ ትሆን ዘንድ በእኔ ትፈርዳለህን?
በእውነት እግዚአብሔር የለም ማለት ድፍረት ነው፡፡ እርሱ በሰራት ትንሽ አይምሮ ያየናቸውን ችግሮች አሰባስበን እግዚአብሔር የለም ማለት በእውነት ትልቅ ድፍረት ነው፡፡ ኦ አምላኬ አለ በእውነት አለ፡፡ አምላኬ እግዚአብሔር እጅግ ታላቅ ነው ልገምተው ከምችለው በላይ ታላቅ ነው፡፡ ብር ስላጣሁ፣ ስራ ስላጣሁ፣ ጤና ስላጣሁ ወይም የሰዎችን ስቃይ ስላየሁ መኖሩን የምክደው አምላክ አይደለም፡፡ እግዚአብሔር በእውነት አለ፡፡ በዙሪያዬ የማየው ችግር ምክንያቱና ውጤቱ ባይገባኝም እግዚአብሔር ግን አለ፡፡ስለዚህ በአምላኬ ፊት ራሴን እንቃለሁ፡፡ እንዲህም እላለሁ ሁሉን ታደርግ ዘንድ ቻይ እንደ ሆንህ፥ አሳብህም ይከለከል ዘንድ ከቶ እንደማይቻል አወቅሁ። በችግር ውስጥ ላለ ሰው ይህን ማለት ቀላል እንዳልሆነ አውቃለሁ ነገር ግን ከዚህ የተሻለ ምላሽ ማግኝትም አይቻልም፡፡ በአጭሩ በህይወታችንና በዙሪያችን በሚሆነው ነገር ሁሉ እግዚአብሔር አዋቂና ትክክል ነው፡፡   
ማጠቃለያ - እና ምን ተስፋ አለን?
በዚህ ክፍል መግቢያ በአዳም ምክንያት አለም እንዴት እንደተረገመች አይተናል፡፡ ነገርግን እግዚአብሔር አምላክ የረገመውን ሰው ያለተስፋ አልተወውም፡፡ ወዲያው የመጀመሪያ የሆነውን ተስፋ ሰጠው ዘፍ 3፡15 በአንተና በሴቲቱ መካከል፥ በዘርህና በዘርዋም መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፥ አንተም ሰኰናውን ትቀጠቅጣለህ። ይህ የተስፋ ቃል ሰይጣንን የሚበቀል ዘር ከሴቲቱ እንደሚወለድ የተሰጠ ተስፋ ነው፡፡ ይመጣል ተብሎ ተስፋ የተሰጠው ኢየሱስ ከምመጣቱ በፊት ግን ብዙ ሺ አመታት አልፈዋል በነዚህ ጊዜያት ውስጥ እግዚአብሔር የተስፋውን ቃል የያዘውን ትውልድ በአስደናቂ ሁኔታ ጠብቋል፡፡ በየመሃሉም ለአባቶች እግዚአብሔር የተስፋ ቃሉን ሲያድስና ሲያሳስብ ኖሯል፡፡ በተለይ ለአብርሃም የምድር አሕዛብ ሁሉም በዘርህ ይባረካሉ፥ ቃሌን ሰምተሃልና።
ታዲያ ይህ ተስፋ በኢየሱስ ክርስቶስ መምጣት ፍፃሜውን አገኝ፡፡ ገላ 3፡13-16
በእንጨት የሚሰቀል ሁሉ የተረገመ ነው ተብሎ ተጽፎአልና ክርስቶስ ስለ እኛ እርግማን ሆኖ ከሕግ እርግማን ዋጀን፤
የመንፈስን ተስፋ በእምነት እንድንቀበል፥ የአብርሃም በረከት ወደ አሕዛብ በኢየሱስ ክርስቶስ ይደርስላቸው ዘንድ።
ወንድሞች ሆይ፥ እንደ ሰው ልማድ እላለሁ። የሰው ስንኳ ቢሆን እርግጠኛውን ኪዳን ማንም አይንቅም ወይም አይጨምርበትም።
ለአብርሃምና ለዘሩም የተስፋው ቃል ተነገረ። ስለ ብዙዎች እንደሚነገር። ለዘሮቹም አይልም፤ ስለ አንድ እንደሚነገር ግን። ለዘርህም ይላል፥ እርሱም ክርስቶስ።
በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ባለ እምነት ከሃጢያት ባርነት ነፃ መውጣትን እና የሃጢያት ስርየትን አግኝተናል፡፡ ነገር ግን ክርስቶስ ከመጣ በኋላም ቢሆን ስቃይና መካራ አልተወገደም ስለዚህ ደግመ የሚቀር ተስፋ አለ ማለት ነው፡፡ ሮሜ 8 ፡ 18-25
ለእኛም ይገለጥ ዘንድ ካለው ክብር ጋር ቢመዛዘን የአሁኑ ዘመን ሥቃይ ምንም እንዳይደለ አስባለሁ።
የፍጥረት ናፍቆት የእግዚአብሔርን ልጆች መገለጥ ይጠባበቃልና።
ፍጥረት ለከንቱነት ተገዝቶአልና፥ በተስፋ ስላስገዛው ነው እንጂ በፈቃዱ አይደለም፤
ተስፋውም ፍጥረት ራሱ ደግሞ ከጥፋት ባርነት ነፃነት ወጥቶ ለእግዚአብሔር ልጆች ወደሚሆን ክብር ነፃነት እንዲደርስ ነው።
ፍጥረት ሁሉ እስከ አሁን ድረስ አብሮ በመቃተትና በምጥ መኖሩን እናውቃለንና።
እርሱም ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን የመንፈስ በኵራት ያለን ራሳችን ደግሞ የሰውነታችን ቤዛ የሆነውን ልጅነት እየተጠባበቅን ራሳችን በውስጣችን እንቃትታለን።
በተስፋ ድነናልና፤ ነገር ግን ተስፋ የሚደረግበቱ ነገር ቢታይ ተስፋ አይደለም፤ የሚያየውንማ ማን ተስፋ ያደርገዋል?
የማናየውን ግን ተስፋ ብናደርገው በትዕግሥት እንጠባበቃለን።
ታዲያ ይህ የቀረ ሊመጣ ያለ ተስፋ ምንድን ነው? የዮሐ ራዕይ 21፡3-4
ታላቅም ድምፅ ከሰማይ። እነሆ፥ የእግዚአብሔር ድንኳን በሰዎች መካከል ነው ከእነርሱም ጋር ያድራል፥ እነርሱም ሕዝቡ ይሆናሉ እግዚአብሔርም እርሱ ራሱ ከእነርሱ ጋር ሆኖ አምላካቸው ይሆናል፤
እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፥ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፥ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፥ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና ብሎ ሲናገር ሰማሁ።
ሃሌሉያ! ታላቁ ተስፋችን ይህ ነው አሁን ካለው ስቃይ ጋር ሊነፃፀር የማችለው ተስፋችን ይህ ነው፡፡ ኢየሱስ ይህን ሊያዘጋጅልን ሄዷል፡፡ ወደዚህ ተስፋም ሊያስገባን ዳግመኛ ይመጣል፡፡ ኦ ምን አይነት ድንቅ ተስፋ ነው፡፡ ምን አይነት አስደሳች ጊዜ ይሆን፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር ማደር፣ ሞት የሚባል ነገር መጥፋት፣ ሃዘንም ሆነ ጩኅት አለመኖር፡፡ ምን አይነት አስደናቂ ጊዜ ይሆን፡፡ ግባችን ይህ ነው፡፡ በሰማይ የተዘጋጀልን ደስታ ይህ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ተስፋም ሙሉ ፍፃሜውን የሚያገኘው ያኔ ነው፡፡

ታዲያ ጥያቄው ይሄ ነው፡- ለዚህ ተስፋ ተዘጋጅታችኋል? ወደዚህ ተስፋ ሁሉም አይገባም፡፡ በክርስቶስ አምነው የዳኑ ብቻ የዚህ ተስፋ ባለርስቶች ይሆናሉ፣ ለዘላለም፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስን ቸል ያሉ ግን ወደ ዘላለም ጥፋት ያመራሉ፡፡ ስለዚህ ተዘጋጅታችኋል፡፡ ዛሬውኑ በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን የዚህ ተስፋ ተቋዳሽ እንድተሆኑ እጋብዛችኋለሁ፡፡ በነገር ሁሉ እግዚአብሔር ይረዳችሁ አሜን፡፡ 
በስተመጨረሻ አንድ መዝሙር ልጋብዛችሁ ክቡር ቀን በዜማ ለክርስቶስ
                                                                                    By Yosef M.