Thursday, May 7, 2015

እውነት እግዚአብሔር አለን?



ክፍል አንድ - እውን ሁሉን ቻይ አምላክ አለ?
የቀድሞው የ CNN Larry King Live አዘጋጅና አቅራቢ ታዋቂው ጋዜጠኛ ላሪ ኪንግ በአንድ ወቅት በቀጥታ ውይይት ለጋበዛቸው የሃይማኖት ሰዎች ያቀረበላቸው ጥያቄ “Where was God on 9/11?” የሚል ቀላል የሚመስል ነገር ግን ሞጋች ጥያቄ ነበር፡፡ በእውነት በህይወታችን ይህን መሰል ጥያቄ ደጋግመን እናነሳለን፡፡ where are you GOD? Why is this thing happening to me? Why don’t you care? Why you let evil to happen? እና ሌሎች ሌሎችም፡፡
"ነገር ሁሉ ለበጎ ነው፡፡" የሚል ጥቅስ በብዙ ሰዎች ቤት ግድግዳ እና በታክሲዎች ውስጥ ጭምር ተፅፎ የምናየው የተለመደ አይነት ጥቅስ ነው፡፡ እራሳችንንም ሆነ ሌሎች ሰዎችን ለማፅናናት ይህችን ጥቅስ ብዙ ጊዜም እንጠቀምባታለን፡፡ ይህን ጥቅስ ለራስም ሆነ ለሌላ ሰው መናገር ግን ሁል ጊዜ ቀላል የማይሆንበት አጋጣሚ ብዙ ነው፡፡ በህይወታችን ከሚያልፈው ከባድ ሁኔታ የተነሳ፤ ነገሮችን ለበጎ እንዲሆኑ ማመን ይቀርና በአምላክ ላይ ማጉረምረምና የት ነው ያለህው? ብለን መጠየቅ የምንጀምርበት አጋጣሚ ብዙ ነው፡፡
መዝሙረኛው ዳዊት በተደጋጋሚ ለምን? ለምን? ለምን? እያለ ይጠይቃል፡፡ በመፅሃፍ ቅዱሳቸችን እንደ ዳዊት በስደትና በችግር የተሰቃየ ሰው ያለ አይመስለኝም፡፡ ለዚህ ነው ዳዊት አንዳንዴ አምላኬ ሆይ ስለምን ርቀህ ቆምክ(መዝ 10፡1)? ሌላ ጊዜ ደግሞ ለምን ተውከኝ(43፡2)፣ሌላ ጊዜ ለምን ረሳህኝ፣ ለምን ፊትህን ከእኔ ትሰውራለህ? እያለ አምላኩን የሚጠይቀው፡፡ ዳዊት በእውነትም ፃድቅ ሰው ስለሆነ በአምላኩ ላይ በድፍረት አልተናገረም፡፡ በእኛ ዘመን ግን ጥያቄው ለምን ከሚል የዘለለ እና የአምላክን ህልውናም ጥያቄ ውስጥ ያስገባ ነው፡፡
አውነት አውነት ሁሉን የፈጠረ፣ ሁሉን ቻይ የሆነ እና ፍጡሩን የሚወድ አምላክ የሚባል ነገር አለ?
ካለስ
ጥያቄ አንድ - ለምን የህመም ስቃይን ይፈቅዳል?
አዲስ አበባ የሚገኝውን የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የልጆች ካንሰር ማእከል የጎበኝ ሰው ምን አይነት የተደበላለቀ ስሜት ውስጥ ሊገባ እንደሚችል ያየ ሰው ያውቀዋል፡፡ ብዙዎቹ አልጋቸው ላይ ተኝተው እጅግ ከባድ ከሆነው ህመማቸው ጋር ሲታገሉ፣ የተወሰኑት ህመማቸውን ለመርሳት ለመጫወት ሲጥሩ፣ የቤተሰብ ሃዘንና ጭንቀት… ሌላም ሌላም፡፡ በእውነቱ በጣም የሚረብሽና ልብን በሃዘን የሚሞላ ቦታ ነው፡፡
ይህን ለምሳሌ ያህል አነሳሁ እንጂ በህይወታን እኛም ሆንን የምነወዳቸው ሰዎች በህመም ስቃይ ውስጥ ስናልፍ አይተናል፡፡ በተለይ የቤተሰብ አባል በህመም ሲሰቃይ ማየት እጅግ ከባድ ነው፡፡ የበለጠ የሚከፋው ደግሞ በማይድን ህመም ውስጥ ሆኖ ሞቱን የሚጠባበቅ ሰው ሲሆን ነው፡፡ ኦ የሚወዱት ሰው ታሞ ሲሰቃይ ከማየት የበለጠ አሰቃቂ ነገር የለም፡፡ ቢያንስ ህመምን እንኳን መካፈል ቢቻል ምንያህል ቀለል ሊል ይችል እንደነበር አስባለሁ፡፡ ነገር ግን አይቻልም፡፡ የሚወዱት ሰው ሲሰቀይ እያዩ ወደ ሞት መሸኝት…
ታዲያ ይህ ሁሉ አሰቃቂ ስቃይ በሰው ልጆች ህይወት ሲያልፍ እውነት እግዚአብሔር የሚባል ሁሉን ቻይ አምላክ አለ? ህፃናት ምኑንም ሳያውቁት በህመም ተሰቃይተው እንደ ልጅ አንድም ቀን ስቀው ተጫውተው ሳይውሉ ወደ ሞት ሲሄዱ በእውነት ለፈጠረው ሩህሩ የሆነ አምላክ አለ? የምንወዳቸው ሰዎች በህመም እያጣጣሩ እና እየተሰቃዩ፤ የቱንም ያል አምነን ወደ አምላክ ብንፀልይም ወደ ሞት ሲሄዱ እውነት እግዚአብሔር አለ ወይ?

ጥያቄ ሁለት - ለምን ችግር እና ረሃብን ይፈቅዳል?
የአዲስ አበባ ጎዳናዎቸን ለተወሰኑ ሰአታት መቃኝት ችግር ማለት ምን ማለት እንደሆነ በደንብ ያስረዳል፡፡ ማታ ማታ ከብርድ ለማምለጥ በየቦታው በቡድ በቡድን እሳት አሙቀው የሚዘምሩ፣ ጠዋት ጠዋት በየስርቻው የተኙ፣ ቀን ቀን ደግሞ የእለት ጉርሳቸውን ፍለጋ ከቦታ ቦታ ለልመና የሚንከራተቱ ህፃናትን ማየት እጅግ የተለመደ የከተማችን ገፅታ ነው፡፡
በአዲስ አበባ ውስጥ ያለ ድህነት ከምንገምተው በላይ ከባድና አስጨናቂ ነው፡፡ አስር እና አስራ አምስት ሜትር በማይሞላ ርቀት ውስጥ ያለ የኑሮ ልዩነት እጅግ አስገራሚ ነው፡፡ ለምግብ፣ ለህክምናና ቤተሰብን ለማስተዳደር ገንዘብ ያጣ ባለበት መንደር በየቀኑ ዘመናዊ መኪናዎችን የሚቀያይሩ ሰዎችም ደግሞ አሉ፡፡ ለአንዲት እናት ለሚያለቅሰ ልጇ ምግብ መስጠት ካለመቻል የበለጠ ምን አሳዛኝ ነገር አለ?
ለእኛ ኢትዮጲያውያን ደግሞ የረሀብና የእጦት ስቃይ በደንብ የሚገባን ጉዳይ ነው፡፡ በእውነቱ እግዚአብሔር የሚባል አምላክ ከነበረ በ77 ድርቅ ያሁሉ ሰው ሲያልቅ የት ነበር? ህፃናት በችግርና በችጋር ከመንደራቸውና ከቤታቸው ተሳደው በየጎዳናው ሲበተኑ አምላክ የት ነው ያለው? እውነት እግዚአብሔር ካለ ሰዎች በችግር ሲሰቃዩ ለምን ዝም ይላል?

ጥያቄ ሶስት - ለምን ማህበራዊ ኢ-ፍትህን ይታገሳል?
ማህበራዊ ኢ-ፍትሃዊነትን በየቦታው የምናስተውለው ጉዳይ ነው፡፡ በሰድሆች ጉልበት እና ላብ ሃብታሞች ይበልጥ ሃብታም ሲሆኑ ድሆች ደግሞ ሲደኸዩ፤ አጭበርባሪዎችና ውሸታሞች ይበልጥ ሲሳካላቸው አምላካቸውን የሚፈሩና የሚያከብሩ ሰዎች ግን ሁልጊዜ በችግር ውስጥ ሲወድቁ የተለመደ የአለማችን እውነታ ነው፡፡ በእውነቱ የሚሳካለት እና የሚቃናለት አምላኩን በመፍራት በፅድቅና ህግን በማክበር የሚመራ ሰው ነው ወይስ በብልጣብልጥ አካሄድ ህግን ለራሱ የሚተረጉም ክፉ ሰው ነው?
እስኪ ቤተክርስቲያን አካባቢ የሚለምኑ አዛውንቶችን ተመልከቱ፡፡ ብዙዎቹ ወጣትነታቸውን እና ጉልበታቸውን ለሌሎች መሳካት እና ውጤት ሲያፈሱ ኖረው በስተመጨረሻ ግን ዞር በሉ የተባሉ ሰዎች ናቸው፡፡ ታዲያ እውነት ፍትህን የሚወድና የሚያደርግ አምላክ አለ? እውነት ፍትህን የሚወድ አምላክ ካለ ሰው እንደ እንስሳ ሲሸጥ ሲለወጥ ባሪያ ሲደረግ የት ነበረ? ለምን ስግብግብ ባለጠጎች ድሆችን በግፍ ረግጠው ይበልጥ ባለጠጋ ሲሆኑ፤ ድሆች ደግሞ በባለጠጎች ግፍ ይበልጥ ድሃ ሲሆኑና መድረሻ ሲያጡ እውነት የሚወዳቸው ሁሉን ቻይ አምላክ አለ?

ጥያቄ አራት - ለምን የሰው እልቂትን ይፈቅዳል?
መቼስ አለማችን በታሪኳ በጦርነቶች የታደለች ነች፡፡ እውነት አምላክ የሚባል ነገር አለ ካላችሁ ሌላው ሌላው ይቅርና በሁለቱ የአለም ጦርነቶች ያሁሉ ሰው እንደዘበት ሲረግፍ ለምን ጣልቃ አልገባም? ሁሉ ይቅርና የእግዚአብሔር ህዝብ ይባሉ የነበሩት አይሁዳውያን በናዚ በግፍ በአሰቃቂ ሁኔታ ሲጨፈጨፉ ለምን ዝም አለ? እነሱም በተራቸው የፍልስጤም ህፃናትን ቤሰበባ ሰበቡ ሲጨፈጭፉ ለምን ዝም አለ? አሁንም በምድራችን በተለያዩ ቦታዎች ጦርነቱ በምን ምክንያት እንደሆነ እንኳን የማያውቁ ንፁሃን ህፃናት፣ እናቶች እና አዛውንቶች ይሰደዳሉ፣ ይሞታሉ ይንገላታሉ፡፡ ታዲያ ለተጎዱት የሚራራ አምላክ አለ? አሸባሪዎች በየጊዜው በጅምላ ንፁሃን ሰዎችን ሲፈጁ፣ ሲያርዱ፣ ሲዘርፉ እና ሲያሳድዱ አምላክ ካለ ለምን ይታገሳቸዋል?
በየጊዜው የመሬት መናወጥ፣ ሱናሚ፣ ጎርፍ የእሳት ቃጠሉ፣ ከፍተኛ ቅዝቃዜ፣ ከፍተኛ ሙቀት… የተለመዱ የመገናኛ ብዙሃን ዜናዎች ናቸው፡፡ በነዚህ ሁሉ አጋጣሚዎች የሰዎች ህይወት እንደዘበት በየቦታው ይረግፋል እኛም በየጊዜው ለዜናዎቹ እማኝ እንሆናለን፡፡ ታዲያ አውን ሁሉን የፈጠረ ሁሉን ቻይ አምላክ ካለ የሰውች በጅምላ መሞት አያሳስበውምን? ካሳሰበው ታዲያ ለምን ጣልቃ አይገባም?



ምናልባት እድሜ ልኩን ሲጋራ ሲያጨስ የኖረ እና የሲጋራ ሱሰኛ የሆነ ሰው በሳንባ ካንሰር ታሞ ቢሞት ያንያህል ላይገርም ይችላል፡፡ ነገር ግን በሉኪሚያ የሚሰቃይ  የአራት አመት ህፃንስ? በወሊድ ምክኒያት ቤተሰቧን በትና የምትሞት እናትስ? በዚህ ምክንያት የሚበተን ቤተሰብ? በኢንዱስትሪ የበለፀጉ ሃገራት በአሲድ ዝናብ ቢቸገሩ ብዙም አስደናቂ ላይሆን ይችላል፡፡ ነገርግን በአመት አንድ ጊዜ አርሶ የሚበላው የሃገሬ ገበሬ በድርቅ ምክንያት ሲራብና ሲሞትስ ምን ይባላል? አገርሰላም ብሎ ከህፃናት ልጆቹ ጋር የሰላም እንቅልፉን የተኛ አባወራ በድንገተኛ መሬት መንቀጥቀጥ ዳግመኛ ላይናሳ እስከወዲያኛው በፍርስራሽ ተቀብሮ ሲያሸልብ ምን ይባላል?
ከላይ የጠቃቀስኳቸውን ጥያቄዎች እና ሌሎቹንም ጥያቄዎች ስንመለከት እውነት አምላክ ወይም ፈጣሪ የሚባል ነገር አለን ብለን እንድንተይቅ ያደርገናል፡፡ እውነት ግን አምላክ የሚባል ነገር አለ?
የህን ጥያቄ በሚቀጥለው ክፍል ለመመለስ እሞክራለሁ እስከዛው እያሰባችሁበት ቆዩኝ
ክፍል ሁለት ይቀጥላል…

No comments: